Sariyose
የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አቋርጦት የነበረውን መደበኛ የህክምና አገልግሎት ሊጀምር ነው
ሆስፒታሉ ሙሉ ለሙሉ የኮቪድ 19 ታካሚዎችን ተቀብሎ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፥ ቀድሞ ይሰጣቸው የነበሩ የህክምና አገልግሎቶችን በአቅራቢያው ወደሚገኙ ጤና ጣቢያዎች አዘዋውሮ አገልግሎት ሲሰጥ ቀይቷል።
ሆስፒታሉ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ አሁን ላይ የኮቪድ ህክምና እና የመደበኛ ህክምና አገልግሎት በጣምራ መስጠት ሊጀምር ነው።
የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ታምሩ አሰፋ፥ የኮቪድ19 ፅኑ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ቁጥር እንደተጠበቀው ባለመሆኑና አብዛኛው ታካሚ በቤቱ ራሱን በመንከባከብ ወይም በሌሎች ማቆያ ቦታዎች እየታከመ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ባለፈም በሌሎች ህመሞች ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ታካሚዎች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የኮቪድ ህክምና እና የመደበኛ ህክምና አገልግሎትን በጥምረት ለመስጠት ማስፈለጉን ተናግረዋል።
ጥምር አገልግሎቱን ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውን የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጁ፥ ባለሙያዎች የተዋቀሩ ሁለት ኮሚቴዎች መቋቋማቸውንም ገልጸዋል።
የሆስፒታሉ ሜዲከል ዳይሬክተር ዶክተር መታሰቢያ መስፍን፥ በሆስፒታሉ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት መጀመሩን ገልፀው በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ሙሉ በሙሉ ወደስራ እንደሚገባም አስታውቀዋል።