የአጤ ሚኒሊክ መታሰቢያ የበአታ ቤተ ክርስቲያን ዕድሣት

Sariyose

የአጤ ሚኒሊክ መታሰቢያ የበአታ ቤተ ክርስቲያን 40 ሚሊየን ብር ከፈጀ ዕድሣት በኋላ የፊታችን ቅዳሜ ይመረቃል።

የአጤ ሚኒሊክ መታሰቢያ የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ሕንጻ ቤተ/ክ ዕድሣት ተጠናቅቆ የፊታችን ቅዳሜ ታኀሣስ 3 ቀን 2013 ዓ.ም ታቦቱ ወደ መንበረ ክብሩ ይመለሳል ተብሏል።

ዕለቱ የበአታ ዓመታዊ ክብረ በእንዲሁም የዐጤ ምኒልክ ሙት አመት መታሰቢያ ነው።
የቤተክርስቲያኑ የልማት ኮሚቴ አባል ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ደምሴ ለጣቢያችን እንደተናገሩት ዕድሳቱ 40 ሚሊየን ብር ገደማ የፈጀ ሲሆን በ1 አመት ተኩል ሊጠናቀቅ የታቀደው እድሳት በኮቪድ ምክንያት ሁለት ዓመት ሊፈጅ ችሏል ብለዋል፡፡

ባዕታ ቤተ ክርስቲያን በንግስተ ነገስታት ዘወዲቱ ለአባቷ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የተሰራች ነች ፡፡
በ1910 ዓ.ም የተሰራችው በዐታ በውስጧ የአጤ ምኒልክ ፣ የእቴጌ ጣይቱ ፣ የንግስተ ነገስታት ዘወዲቱ እና የመጀመርያው ግብፃዊው ጳጳስ የአቡነ ማቲያስ መካነ መቃብርም መገኛ ነች፡፡

በቤተክርስትያኗ ውስጥ የሚገኘውና በቅርስነት የተመዘገበው ሙዚየም በውስጡ ፣ አባቶቻችን አድዋ ይዘውት ከዘመቱት መስቀል አንስቶ እስከ ከማይክል አንጄሎ ለአጤ ሚኒልክ የተበረከተ ኦርጂናል ስዕል ፣ ከውጪ ነገስታት ለአፄ ሚኒሊክ የተላኩ ስጦታዎችና የተለያዩ ቅርሶች ይገኝበታል፡፡

የአጤ ምኒሊክ ፀሎት ቤት የነበረችው ፀሎት ቤት ኪዳነ ምህረትም በጊቢው ውስጥ ትገኛለች፡፡
ህንፃ ቤተ ክርስትያኗ ሙሉ በሙሉ በድንጋይ ነው የተሰራቸው፤ እንዳሰራሩ ከሆነ ለብዙ ክፍለ ዘመናት ይቆይ የነበረ ህንፃ በአያያዝ ጉድለት፣ በትኩረት እጦትና በጥገና ስህተት ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስበት ችሎ ነበር፡፡

ጉልላቷ በአጼ ምኒልክ ዘውድ ትዕምርት የተሰራ ሲሆነ የጉልላቱ መሰነጣጠቅ፣የምሶሶዎቹ እግሮች መበላትና ሌሎችም ጉዳቶች ወደ ቤተክርሰቲያኗ ውሃ ሰርጎ እንዲገባና ህንፃው የመፍረስ አደጋ እንዲጋረጥበት አድርጎ ነበር ፡፡
ስዕሎች፣ብራና መፃህፍትና መሰል ቅርሶችም ጉዳት ደርሶባችዋል፡፡
ከፍተኛ የምእመናን ርብርብ የታየበት ስራ ነው የሚሉት የልማት ኮሚቴው አባል ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ደምሴ በመላው አለም ያሉ የበአታ ልጆችና ሚዲያዎች ቅርሱ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስበት አስችሏል ብለዋል፡፡

ቅርሱ ከከፋ ጉዳት ለማዳን ርብርብ ላደረጉ ሁሉ በገዳሙና በእግዚአብሔር ስም ምስጋናቸዋን ያቀረቡ ሲሆን ቅዳሜ በአሉን ሁሉም ቦታው ተገኝቶ እንዲያከብር ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡