የጥፋት ተልእኮ ለመቀበል የተደራጀ አንድ ለ20 የሚል ቡድን በምርመራ ማግኘቱን አስታወቀ

Sariyose

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከህወሓት እና ኦነግ ሸኔ ቡድኖች የጥፋት ተልእኮ ለመቀበል የተደራጀ አንድ ለ20 የሚል ቡድን በምርመራ ማግኘቱን አስታወቀ።




  በኮሚሽኑ የወንጀል ምርመራ ቢሮ አገኘሁት ያለውን መረጃ ያብራራው በእነ ሜጀር ጄነራል ገብረ መድህን ፍቃዱ 7 ተጠርጣሪዎች እና በእነ ብርጋዴር ጄነራል አሊጋዝ ገብሬ 4 ተጠርጣሪዎች የተካተቱባቸውን የምርመራ መዝገቦች ለፍርድ ቤት ባቀረበበት ወቅት ነው።

ፖሊስ በእነ ሜጀር ጄነራል ገብረ መድህን ፍቃዱ መዝገብ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀደም ሲል በሰጠው የምርመራ ጊዜ ከተጠርጣሪዎች አገኘሁ ካላቸው መረጃዎች አንዱ ከሕወሓት አመራሮች ተልእኮ በመቀበል የሰሜን እዝ ኔትወርክ ተቋርጦ የመከላከያ ሠራዊቱ እንዲመታ ስለማድረጋቸው የሚያስረዱ የምስክሮችን ቃል መቀበል የሚለው ይጠቀሳል።

ተጠርጣሪዎቹ ከኦነግ ሸኔ አመራሮች ጋርም ግንኙነት ሲያደርጉ እንደነበር የሚያስረዱ ምስክሮችን ቃል ስለመቀበላቸውም ተሰምቷል። በሌላ በኩል ችሎቱ የመከላከያ አካዳሚ ኮሌጅ አመራር የነበሩ እነ ብርጋዴር ጄነራል አሊጋዝ ገብሬ ላይም መሰል የምርመራ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጿል።

በሁለቱም የምርመራ መዝገቦች አዲስ አበባ ውስጥ በኅቡዕ ድብቅ የፖለቲካ እና የጥፋት አጀንዳ በሚያራምደው እና 1 ለ 20 በሚል በተቋቋመው ቡድን ውስጥ ዐሥራ አንዱም ተጠርጣሪዎች የነበራቸውን ተሳትፎ ፖሊስ ለችሎቱ ገልጿል።በሌላ በኩል በሁለቱም የምርመራ መዝገቦች የሚገኙ ተጠርጣሪዎች የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን በማንሣት የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፖሊስም ዋስትናውን በመቃወም መከራከሩን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር የሚመራው ችሎትም በእነ ሜጀር ጄነራል ገብረ መድህን ፍቃዱ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነገ ታኅሣሥ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ሲይዝ በእነ ብርጋዴር ጄነራል አሊጋዝ መዝገብ ላይ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት 12 ቀናት ፈቅዷል ሲል ኢትዮ fm ዘግቧል።