በአዲስ አበባ የሽብር አደጋዎችን ለማድረስ እቅድ የነበረው የህወሀት ቡድን የጸጥታ ሀይሉ ቁጥጥር ሲጠነክርበት በየቦታው የጣላቸው ቦንቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ የፌደራል ፖሊስ አሳሰበ።
በአዲስ አበባ የሽብር አደጋዎችን ለማድረስ እቅድ የነበረው የህወሀት ቡድን የጸጥታ ሀይሉ ቁጥጥር ሲጠነክርበት በየቦታው የጣላቸው ቦንቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ የፌደራል ፖሊስ አሳሰበ።
በመሆኑም ህብረተሰቡ የወደቁ ነገሮችን ሲያይ ለጸጥታ አካላት እንዲጠቁም እና ህጻናትን እንዲጠብቅ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።
እስካሁን በአዲስ አበባ የህውሀት ቡድን በጣሉት ቦምብ አምስት ህጻናት ጉዳት እንደደረሰባቸው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አረጋግጧል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው በተለምዶ 02 ወይም ካፒቴን ደምሴ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ህፃናት ወድቆ ያገኙት ቦንብ እጃቸው ላይ ፈንድቶ ጉዳት እንደደረሰባቸው አሳውቋል።
በዚህም መሰረት አራቱ ህጻናት መጠነኛ ጉዳት አስተናግደው የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ህክምና አግኝተው ወደ ቤተሰቦቻቸው ተቀላቅለዋል ተብሏል፡፡
አንደኛው ህጻን ግን ጉዳቱ ከፍተኛ ስለሆነ በሚኒሊክ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገለት እንደሚገኝ ነው የተነገረው፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊ አቶ ጄይላን አብዲ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት የህውሀት ቡድን በአዲስ አበባ ሽብር ለመፍጠር ቢንቀሳቀስም ቁጥጥሩ ሲጠነክርበት ቦምቦቹን በየቦታው እየጣሉ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
እስካሁን እነዚህ ቡድኖች በሁለት ቦታ በጣሉት ቦምብ ስድስት ሰው ላይ ጉዳት ደርሳልም ብለዋል አቶ ጄይላን፡፡
የህውሀት የጥፋት ቡድኖች በየቦታው ያሰማሯቸው ሰዎች በተለያዩ ቦታዎች የጣሉዋቸው ቦምቦች ሊኖሩ ስለሚችሉ አሁንም ወላጆች ለልጆቻቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ተብሏል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ የተጣሉ እና የተቋጠሩ ነገሮችን በሚያገኝበት እና እየጣሉ የሚገኙ ሰዎችን በሚመለከትበት ጊዜ ለፖሊስ ጥቆማ መስጠት አለበት ተብሏል፡፡
ማንኛውም የከተማው ነዋሪ የተጣለ ነገር ከማንሳቱ በፊት በ991 እንዲሁም በነጻ የስልክ መስመር 011 111 01 11 ላይ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ደውሎ ማሳወቅ ይችላል፡፡
እንደዚሁም በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በ987 ወይም በቀጥታ የስልክ መስመር 011 551 80 00 ላይ ጥቆማቸውን ማድረስ ትችላላችሁ ተብሏል።