ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ አበባ ከተማ ከሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጅ ባለሀብቶች ጋር ተወያዩ


ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ አበባ ከተማ ከሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጅ ባለሀብቶች ጋር ተወያዩ ።


በውይይቱ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የፌደራል መንግስት በህውሃት አጥፊ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ህግን ለማስከበር በመሆኑ ዘላቂ ሰላምን ለማስጠበቅ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል ።

ፅንፈኛው ቡድን ህዝቡን ሽፋን በማድረግ የራሱን ጥቅም ሲያሳድድ መኖሩን እና ጥፋቶችን ሲያቀነባብር መቆየቱን የገለጹት ወ/ሮ አዳነች ችግሩ እዚህ ደረጃ እንዳይደርስ የፌደራል መንግስቱ ከመጀመሪያ ጀምሮ በውይይት ለመፍታት ሰፊ ጥረት ማደረጉን ተናግረዋል ።

ከምንም በላይ ከፊታችን ያለው ጊዜ የአንድነት ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ በከተማዋ የሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆች ከመላው ኢትዮጵያዊያን እህት ወንድሞቹ ጋር በመሆን ለከተማዋ ዘላቂ ሰላምና እድገት በጋራ መስራት አለበት ብለዋል።

የፌዴራል መንግስት በህወሃት ጁንታ ላይ የህግ ማስከበር ስራ በትግራይ ህዝብ ላይ የተለየ ጭቆና እንደ ተፈጸመ ተደርጎ ለሚናፈሰው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ  ጆሮ ሳይሰጥ ለእውነት በመቆም የጥፋት ሀይሉን ተግባር ማውገዝ ይገባዋል ብለዋል ።

በውይይቱ የተሳታፋ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የትግራይ ባለሀብቶች በበኩላቸው በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተደረገውን ጥቃት ማውገዛቸውን ገልጸው መንግስት የሚወስደው ህግን የማስከበር እርምጃ መጠናከር እንዳለበት፤ ለንጹሃን የትግራይ ተወላጆች እንደረስላቸው ህዝቡም በትግራይ ተወላጆች እና በህውሃት መካከል ያለውን ልዩነት ሊረዳ ይገባል ብለዋል ።

በከተማዋ በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ የተለየ ጫና እንዳይፈጠር ከነዋሪው ጋር ተቀራርቦ መነጋገርና መረጃ መለዋወጥ  በኩል የከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እንዲሰራ ተናግረዋል::

አዲስ አበባ ከተማ ሰላሟ ተጠብቆ እድገቷ እንዲፋጠን የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገልፀው በትግራይ የሚኖሩ እህት ወንድሞቻቸው ነጻ እንዲወጣ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል ።

በከተማዋ ነዋሪ በሆኑ  የትግራይ ተወላጆች ላይ ምንም አይነት አድልኦ እና መገለል አሁንም ወደ ፊትም እንደማይደርስ ነገር ግን ህግ የማሰከበር ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ተሳታፊ ለሆኑ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ባለሀብቶች ገልጸዋል ።

በውይይቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አዱኛ ደበላ  እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡